Colossians 3
የማሽን ትርጉም፡ እስካሁን ወደ ቋንቋህ ምንም የታተመ የዚህ መጽሐፍ ትርጉም የለም።
1እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ፥ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ ያለውን እሹ።
2በላይ ያለውን አስቡ እንጂ በምድር ያለውን አይደለም።
3ሞታችኋልና፥ ሕይወታችሁም በእግዚአብሔር ውስጥ ከክርስቶስ ጋር ተሰውሮአልና።
4ሕይወታችሁ የሆነ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ፥ እናንተ ደግሞ በዚያን ጊዜ ከእርሱ ጋር በክብር ትገለጣላችሁ።
5እንግዲህ በምድር ያሉቱን ብልቶቻችሁን ግደሉ፤ ዝሙትንና ርኵሰትን፥ ፍትወትንም፥ ክፉ ምኞትንም፥ ጣዖትን ማምለክ የሆነውን መጎምጀትንም።
6በእነዚህም ምክንያት የእግዚአብሔር ቍጣ በማይታዘዙ ልጆች ላይ ይመጣል።
7እናንተም ደግሞ ከእነርሱ መካከል በኖራችሁ ጊዜ፥ አስቀድሞ በእነዚህ ተመላለሳችሁ።
8አሁን ግን እናንተ ደግሞ ቍጣን፥ ንዴትን፥ ክፋትን፥ ከአፋችሁም ስድብን የሚያሳፍርንም ንግግር፥ እነዚህን ሁሉ አስወግዱ።
9እርስ በርሳችሁ ውሸት አትነጋገሩ፥ አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋር ገፋችሁታልና፥
10በፈጣሪው ምሳሌ ዕውቀትን ለማግኘት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ለብሳችሁታል፤
11በዚያም የግሪክ ሰው አይሁዳዊም የተገረዘም ያልተገረዘም አረመኔም እስኩቴስም ባሪያም ጨዋም መሆን የለም፥ ነገር ግን ክርስቶስ ሁሉ ነው፥ በሁሉም ነው።
12እንግዲህ እንደ እግዚአብሔር ምርጦች፥ ቅዱሳን ሆናችሁ የተወደዳችሁም፥ የምሕረትን አንጀት፥ ቸርነትን፥ ትሕትናን፥ የዋህነትን፥ ትዕግሥትን ልበሱ፤
13እርስ በርሳችሁ ተቻቻሉ፥ ማንም በባልንጀራው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖረው ይቅር ተባባሉ፤ ጌታ ይቅር እንዳላችሁ እናንተም እንዲሁ አድርጉ።
14በእነዚህም ሁሉ ላይ የፍጹምነት ማሰሪያ የሆነውን ፍቅርን ልበሱት።
15በአንድ አካልም የተጠራችሁለት የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይግዛ፤ አመስጋኞችም ሁኑ።
16የክርስቶስ ቃል በሙላት ይኑርባችሁ፤ በጥበብ ሁሉ እርስ በርሳችሁ አስተምሩና ገሥጹ፤ በልባችሁም ለእግዚአብሔር በጸጋ በመዝሙርና በውዳሴ በመንፈሳዊም ቅኔ ዘምሩ።
17በቃልም ቢሆን ወይም በሥራ የምታደርጉትን ሁሉ፥ በእርሱ በኩል እግዚአብሔር አብን እያመሰገናችሁ፥ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት።
18ሚስቶች ሆይ፥ በጌታ እንደሚገባ ለባሎቻችሁ ተገዙ።
19ባሎች ሆይ፥ ሚስቶቻችሁን ውደዱ፥ መራራም አትሁኑባቸው።
20ልጆች ሆይ፥ ይህ ለጌታ ደስ የሚያሰኝ ነውና በሁሉ ለወላጆቻችሁ ታዘዙ።
21አባቶች ሆይ፥ ልባቸው እንዳይዝል ልጆቻችሁን አታበሳጩአቸው።
22ባሪያዎች ሆይ፥ በቅን ልብና ጌታን በመፍራት እንጂ፥ ለሰው ደስ እንደሚያሰኙ ለታይታ ብቻ ሳይሆን፥ በሥጋ ጌቶቻችሁ ለሆኑት በሁሉ ታዘዙ።
23የምታደርጉትን ሁሉ፥ ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታደርጉ በፍጹም ልባችሁ አድርጉት፤
24ከጌታ የርስትን ብድራት እንድትቀበሉ ታውቃላችሁና፤ የምታገለግሉት ጌታ ክርስቶስ ነውና።
25የሚበድልም የበደለውን ይቀበላል፥ ለሰው ፊትም አድልዎ የለም።
WEBREATH · 11:11
«He himself gives everyone life and breath and everything else» — Acts 17:25
Breath is one for all: everyone lives by it, whoever they are and whatever they believe. Every day at 11:11 local time people stop for sixty seconds, breathe, and thank GOD for the breath — each in their own words, each within themselves. In that minute we are One Breath.
WEBREATH — the Minute at 11:11, your own local time — we are One Breath